About The Region የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በክልሉ መንግሥት የሚተዳደሩ 37 ሆስፒታሎች፣ 285 ጤና ጣቢያዎች፣ 1,464 ጤና ኬላዎችና 206 የግል ክሊኒክ (ሁሉም ደረጃ)፣ 29 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች፣ 66 የግል ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች፣ 2 መምህራን ትምህርት ኮሌጆች፣ 1 የጤና ኮሌጅ እና 2,350 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (ከ1-8)፣ 305 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (9-12) ይገኛሉ። እንደዚሁም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚተዳደሩ 203 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (ከ1-8) እና 20 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች (9-12) ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ባህልና ቋንቋ ክልሉ የበርካታ ባህልና ቋንቋ ብዝሃነት ባለቤት ሲሆን 32 ብሔረሰቦች በጋራ ተከባብረው የሚኖሩበት የብልጽግና ተምሳሌት ክልል ነው፡፡ የእነዚህ ብሔረሰቦች ቋንቋ በአብዛኛው ኦሟዊ፣ ኩሻዊ እና ኒሎሳራዊ ቋንቋ ቤተሰብ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ክልሉ ለመስኖ፣ ለሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ለዓሳ እርባታ አገልግሎት የሚውሉ ወንዞች፣ ሀይቆች እና ለቱሪስት መስህብነት የሚያገለግሉ በርካታ ፏፏቴዎች የሚገኙበት ሲሆን ለቱሪዝም አገልግሎትና ለብዝሃ-ህይወት ጥበቃና ልማት ከፍተኛ ጠቃሜታ ያላቸው ብሔራዊ ፓርኮችም ባለቤት ነው፡፡ አስተዳደራዊ መዋቅር በአስተዳደራዊ መዋቅሩም በዞን፣ በወረዳ፣ በከተማ አስተዳደሮችና በቀበሌዎች የተደራጀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ12 ዞኖች፣ በ65 ወረዳዎች፣ በ33 የከተማ አስተዳደሮች እና በ1,498 ቀበሌዎች (1,268 ገጠርና 230 ከተማ) ናቸው፡፡ ክልሉ 49,235.78 ስ.ኪ.ሜ የሚሸፍን ሲሆን ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 4.4 በመቶውን ይይዛል። የሕዝቡን ብዛት በተመለከተ በ1999 ዓ.ም የብሔራዊ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ዉጤት መረጃ ፕሮጀክሽን መሠረት በሐምሌ 2015 ዓ.ም 8,411,642 ሲሆን ይህም ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 7.73 በመቶውን ይይዛል። የክልሉ አማካይ የህዝብ ጥግግት 176 ሰዎች በካ.ኪ. ሜ እንደሚሆን ይገመታል ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ የክልሉ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ በ4° 20'- 8° 20' ሰሜን ላቲትዩድ (ኬክሮስ) እና 35° 40'-38° 40' ምሥራቅ ሎንግቲውድ (ኬንትሮስ) ይገኛል፡፡ ክልሉ ከጎረቤት ሀገር በደቡብ ከኬንያና በደቡብ ምዕራብ ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም በምዕራብ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምስራቅ ከሲዳማ፣ በሰሜንና በምስራቅ ከኦሮሚያ እና በሰሜን ምዕራብ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ጋር ይዋሰናል። ክልሉ የተለያዩ ስነ-ምህዳር (Ecology) የተፈጥሮ ሀብቶችንና ሁሉንም የአየር ንብረቶች ማለትም ደጋ፣ ወይና ደጋ እና ቆላ የአየር ንብረቶች የያዘ በመሆኑ የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን ለማከናወንና ለኑሮ ምቹ ነው፡፡